Monday, December 16, 2013

ያልተመለሰው የመሬት ጥያቄ


ያልተመለሰው የመሬት ጥያቄ

የመሬት ለአራሹ ህዝባዊ ጥያቄበኢትዮጵያ አደባባዩች መስተጋባት ከጀመረ ዘንድሮ አርባኛ አመቱን 
ደፍኗል፡፡ መሬትን ለጥቂት የስርዓቱ ታማኞች በማደል የሚበዛውን ህዝብ ጭሰኛ ያደረገው ፊውዳላዊው ስርዓት በተነሳበት የመሬት ጥያቄ ከርሰ ምድር ከገባ በኋላ መሬት ለአራሹን ጥያቄው 
እንዳደረገ የገለጸው ደርግ የመሬት ለአራሹን አዋጅ ቢያወጣም ጥያቄው ከማጭበርበሪያነት ሊያልፍ አልቻለም፡፡ደርግ ከአጼው ደጋፊዎች የቀማውን መሬት በአንዳንድ ቦታዎች ለገበሬዎች እጅግ በወረደ የሽንሸና ስልት በማከፋፈል መሬትን ለገበሬው በመስጠት ጥያቄውን የመለሰ ቢመስልም ገበሬውን የስርዓቱ ታማኝ በማድረግ ለማቆየት መሬቱን መያዝ ጥያቄ የሌለው አማራጭ በማድረግ በማየቱ አዋጁ ከፖለቲካ መጠቀሚያነት አላለፈም፡፡ብሶት እንደወለደው የነገረን ኢህአዴግ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ደርግ የወረሳቸውን መሬቶች ለባለቤቶቹ በመመለስ በትግራይ ምልክቶችን በማሳየት ህዝቡን የመሬት ባለቤት ለማድረግ እንደሚታገል ቢያሳይም አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በመሬት ጉዳይ ከቀድሞው መንግስት የተለየ አለመሆኑን ለማሳየት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ በ1987 የአገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ በመሆን የጸደቀው ህገ መንግስት መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ መሆኑን ደንግጓል፡ የስርዓቱ መሪ የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹መሬት የሚሸጠው በኢህአዴግ ቀብር ላይ ነው›› በማለት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ህገ መንግስቱ ለአንድ ፓርቲ ብቻ 
ሳይሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የሚገዙበት መሆኑ እየታወቀ እነ መለስ የድርጅታቸውን እምነት በህገ 
መንግስቱ እንዲካተት ማድረጋቸው ብዙዎችን ሲያስገርማቸው ቆይቷል፡፡ኢህአዴግና ህገ መንግስቱ መሬት የማይሸጥ መሆኑና ንብረትነቱም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነው በማለት ቢደነግጉም መንግስት የተባለው አካል መሬትን እጅግ በወረደ ዋጋ እያከራየ ይገኛል፡፡ መንግስት ኪራይ የሚፈጽምላቸው ካምፓኒዎች መሬቱን የሚረከቡት በመሬቱ ላይ ሰፍረው የነበሩ ዜጎችን አስነስተው መሆኑም መሬት የህዝብ ነው የሚለውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡መሬት የብሄር ብሄረሰቦችና የህዝቦች ነው የሚለው የጆሴፍ ስታሊን አክሳሪ ፍልስፍና መሬት ላይ ሲወርድ መሬት የህዝብ አለመሆኑ በግልጽ ይታያል፡፡ መሬት የህዝብ አለመሆኑንና ሆኖም እንደማያውቅ ከልማት ጋር በተያያዘ እየተፈጸመ ያለውን እውነታ እንመልከት፡፡ በኢትዮጵያችን የመሬት ባለይዞታነት መብት በገዢዎች ፈጽሞ የማይታወቅ ነው፡፡ መንግስት ለልማት 
እፈልገዋለሁ የሚለውን መሬት ከባለይዞታዎቹ ለመውሰድ የሚጠይቀው ጊዜ የሶስት ወራት እድሜ ብቻ ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች በአስራ አምስት ቀን ዕድሜ ይዞታቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ የተነገራቸው ዜጎች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ “መሬት የህዝብ ነው ይዞታችንን አንለቅም” ያሉ ዜጎች በመሬቱ ላይ ያለው ንብረታቸው በአፍራሽ ግብረ ሃይል ፈርሶ የአፍራሾቹን ወጪ እንዲከፍሉ ተደርገዋል፡፡ከልማቱ ባሻገር የምንሰማው ነገርም ህዝብ የሚባለው አካል መሬት አልባ መሆኑን ነው፡፡ ከተወለደበት ክልል ውጪ የመኖር፣ንብረት የማፍራትና ቤተሰብ የማፍራት መብት እንዳለው በህገ መንግስቱ የተረጋገጠለት ዜጋ በጎሳ ፖለቲካ በታወሩ ሃይሎች “ክልላችንን ለቅቀህ ውጣ” ሲባል ለመፈናቀል ይዳረጋል፡፡ ከዚህ ቀደም በ አ ር ሲ ፣ በ አ ፋ ር ፣ በ ቤ ኒ ሻ ን ጉ ል ና በጉራፈርዳ የደረሱ መፈናቀሎችን መመልከት እንችላለን፡፡ ህዝቡ መሬት ቢኖረው ከክልሌ ውጣ በሚል የዘረኞች ፖለቲካ ለመፈናቀል አይዳረግም ነበር፡፡አቶ ደሳለኝ ራህመቱ በኢትዮጵያ የመሬት ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥናቶችን በማቅረብ የገዘፈ ስም አካብተዋል፡፡ ደሳለኝ የኢትዮጵያ መንግስታት መሬትን በተመለከተ በአብዛኛው ተመሳሳይ አቋም ለምን እንደሚያራምዱ ሲያብራሩ ‹‹ከህዝቡ ከ80 በመቶ በላይ ኑሮውን የመሰረተው ከመሬት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ገበሬው መሬቱን ከያዝክበት የትም ሊነቃነቅ 
እንደማይችል መንግስታቱ ስለሚገነዘቡ መሬቱን በመስጠት ገበሬው አቅሙን እንዲያዳብር አይፈቅዱለትም›› ይላሉ፡፡ዛሬም መሬትን የተመለከቱ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ መሬቱን የተቆጣጠረው መንግስት ሃብታምና የደረጀ ሲሆን ከኩርማን መሬት ጋር የተጣበቀው ገበሬ ከኑሮ ጋር ግብግብ እየገጠመ ከባርነት ያልተለየ ህይወት ይገፋል፡፡ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በመንግስት የተመራ ኢንቨስተር ወደ ቀዬው በመምጣት ኩርማን 
መሬቱን ሊነጥቀውና የነገ ህይወቱን ለልመና ሊዳርገው እንደሚችል በማሰብ ቀኑን በጭንቀት ተውጦ ያሳልፋል፡፡ ገበሬው የመሬት ባለቤት የሚሆንበትና መሬቱን እንደየትኛውም ሸቀጥ በገበያ ዋጋ የሚሸጥበት ስርዓት እስኪዘረጋና የዜጎች የይዞታ ባለቤትነት መብት እስኪረጋገጥ የመሬት ጥያቄው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ 

No comments:

Post a Comment