Tuesday, December 17, 2013

አና ጐሜዝ ስለተቃዋሚዎች የተሻለ የአቋም ለውጥ አላደረገችም”ዶ/ር መረራ ጉዲና

“አና ጐሜዝ ስለተቃዋሚዎች የተሻለ የአቋም ለውጥ አላደረገችም”ዶ/ር መረራ ጉዲና


Merera-Gudina
ከአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ተወካዮች ጋር ከተገናኙትና ውይይት ካደረጉት መካከል ዶ/ር መረራ ጉዲና አንዱ ናቸው፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ከሎሚ አዘጋጅ ቶማስ አያሌው ጋ ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡- ሎሚ፡- ከአውሮፓ ህብረት ተወካዮች ጋር መገናኘታችሁና ውይይት ማድረገችሁ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ ቢገልፁልን;ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ ቢገልፁልን; ዶ/ር መረራ፡- ጀአጠቃላይ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምህዳር፣ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የፖለቲካ ምህዳሩ አደገኛ በሆነ መንገድ እየጠበበ መምጣቱን፣ ነገሮች ወደኋላ መጓዛቸውን፣ መሠረታዊ የመንግስት ተቋማት የአንድ ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚ መሆናቸውን፣ ፓርላማው፣ ምርጫ ቦርዱ፣ ሚዲያውም ሙሉ በሙሉ በሚባልበት መልኩ በአንድ ፓርቲ ስር መሆናቸውን ገልጸናል፡፡ሠላማዊ ሰልፎችን፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማካሄድ ችግር እንደፈጠረብን፣ በሀገሪቱ ውስጥ ለመንቀሣቀስ ችግር እንደገጠመን በስፋት አስረድተናል፡፡ ስለእረኞች ጉዳይ በስፋት አንስተናል፡፡ ሉዊ ሚሼል የሚባለው የእርዳታ ሰጪ ኃላፊውና አንድ ሌላ ሰው እስረኞችን ገብተን እንድናይ ተፈቅዶልናል ሲሉ ገልፀውልናል፡፡ ፓርላማ ውስጥ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድ ተወካይ ብቻ መኖሩን ይገልፁ ነበር፡፡ ከ97 ምርጫ የተዘረፈው ተዘርፎ የተረፈው 170 መቀመጫ ነበረን፡፡ ይሄን በማነፃፀር ተገልፆላቸዋል፡፡ አጠቃላይ እንግዲህ ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትም ሆነ ስርዓትን ለመገንባት ሀሣብ እንደሌለው ለማስረዳት ሞክረናል፡፡ ሎሚ፡- እናንተን ያናገሩት የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች ምን ዓይነት አቋም ነበራቸው; ዶ/ር መረራ፡- በአጠቃላይ እኛን ለመስማት ነበር የጠሩን፡፡ እንዲያውም እኔን ጨምሮ አጥብቀን ያነሣነው ሀሳብ፣ ገንዘብ ስትሰጡ ስለ ሰብአዊ መብቶችና ሌሎች ጉዳዮች አታነሱም የሚል ነበር፡፡ ለእሱ ጥያቄ አንዱ የአውሮፓ ፓርላማ አባል እዚህ አዲስ አበባ ያለውን ተወካይ ጠየቀው፡፡ አንዷ የአውሮፓ ሕብረቱ ምክትል ተወካይ እሷም ከዚህ በኋላ አንዳንድ ነገሮችን እናደርጋለን ለማለት ሞክራ ነበር፡፡ እኛ ግን ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወዲህ ትላልቅ የሚባሉት የአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ተቃዋሚዎችን ሲሸሹ እንደነበር አስረድተናል፡፡ እኛ የምንለውን ነገር ነበር እነሱ በጥሞና ሲያዳምጡ የነበሩት፡፡ ሎሚ፡- ተቃዋሚዎች ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ ነው የሚል ሀሳብ አላነሱላችሁም; ዶ/ር መረራ፡- ጠይቀውናል፤ ምን እየሰራችሁ ነው? ምህዳሩ እንዴት ነው? እንዴት እየሰራችሁ ነው? ብለው ጠይቀውናል፤ መልሰንላቸዋል፡፡ ሎሚ፡- ምላሻችሁ ምን ነበር; ዶ/ር መረራ፡- ተቃዋሚዎች መስራት የምንችለውን እየሞከርን ነው ያለነው፡፡ የተቃዋሚ ህብረትም እንደ መድረክ ዓይነቱ ምን እየሞከረ እንደሆነ አስረድተናል፡፡ እነሱ የሚጠይቁን “ለምን አንድ አልሆናችሁም” ስለሆነ አንድ ለመሆን እየተሞከረ እንዳለ ለማስረዳት ሞክረናል፡፡ ሎሚ፡- የዛሬ ዘጠኝ አመት ወ/ሮ አና ጐሜዝን በደንብ ያውቋቸዋል፡፡ ከዘጠኝ አመት በኋላ እንደመገናኘታችሁ መጠን ምን አዲስ ነገር ተመልከታችሁ? ወ/ሮ አና ጐሜዝ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያላቸው አቋም ምን ይመስላል; ዶ/ር መረራ፡- አና ጐሜዝ ከእኛ ተቃዋሚዎች የተሻለ የአቋም ለውጥ አላደረገችም፡፡ የዛን ጊዜም ምርጫ እንደተጭበረበረ ለማስረዳት ሞክራለች፡፡ አሁንም ቢሆን ተቃዋሚዎች ችግር ላይ እንደሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ እንደሄደ ከሞላ ጐደል አስረድታለች፤ አዲስ አቋም ግን አላሣየችም፡፡ ድሮ የገፋችበትን አቋም አጠናክራ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር የፖለቲካ ምህዳር መስፋት በዋናነት አስፈላጊ መሆኑን፣ በዚህ አቅጣጫ የአውሮፓ መንግስታትም መስራት እንዳለባቸው ገልፃለች፡፡ በ1997 ዓ.ም. ከነበራት አቋሟ የተለየ ለውጥ አላሣየችም፡፡ ሎሚ፡- ወ/ሮ አና ጐሜዝ “ጠ/ሚ መለስ ቢኖሩ ኖሮ ወደዚህ ሀገር አልገባም ነበር፡፡ ከዛም ባለፈ የጠ/ሚ መለስ አለመኖር ለውጥ ይፈጥራል” ብለው ተናግረዋል; ዶ/ር መረራ፡- ይሄንንም አንስተዋል፤ ለምሣሌ፡- ጠ/ሚ መለስ ቢኖር ወደዚህ አልመጣም ነበር፤ እናንተስ ጋ ምን ለውጥ አለ? ብለው ጠይቀውናል፡፡ እኛ ጋ ለውጥ ካለ ወደፊት ሣይሆን ወደኋላ የመሔድ ለውጥ ነው፡፡ የምርጫ ጉዳይ የፖለቲካ ምህዳር ጉዳይ፣ የመንግስት ተቋማት ጉዳይ፣ የሚዲያ ጉዳይ…ምንም ለውጥ የታየባቸው መስኮች እናዳልሆኑ አስረድተናል፡፡ ምንም የፖሊሲ ለውጥ እንዳላየን ለማስረዳት ሞክረናል፡፡ ሎሚ፡- እናንተን ካናገሩ በኋላ የመንግስት ባለስልጣናትን አናግረዋል; ዶ/ር መረራ፡- ይመስለኛል፡፡ ፈቃድም ስላገኙ፣ ከዛ በኋላም መልሰው ሊያናግሩ ይችላሉ፡፡ ያናገሩም ይመስለኛል፡፡ ለምሣሌ እስር ቤት (ቃሊቲን) ለማየት ፈቃድ ያገኙት ከዛ በፊት ነው፡፡ ሁለት የእኛ አመራሮች ፈቃድ አግኝተዋል ነው ያሉት፡፡ ከዛ በፊት እና በኋላ ማንን እንዳናገሩ አናውቅም፡፡ ግን የተወሰኑትን የመንግስት ባለስልጣናት ማናገራቸውን ከንግግራቸው መገመት ይቻላል፡፡ ሎሚ፡- ካደረጋችሁት ውይይት አንፃር ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠይቁት ጥያቄ ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር መፍትሄ ሊያገኙ ይችላሉ; ዶ/ር መረራ፡- ይሔ በሁለት ዓይነት መልኩ የሚታይ ነው፡፡ እኛም የቤት ስራዎቻችንን መስራት የግድ ነው፡፡ የጋራ የፖለቲካ አጀንዳን በሰከነ መንገድ መግፋት፣ የተቃዋሚዎችን አቅም የመገንባቱ እነዚህ፣እነዚህን የቤት ስራዎች ካልሰራን ፈረንጆች ራሣቸው የረዷቸውን ሰዎች ነው የሚረዱት፡፡ እራሣችንን ካልረዳን እግዚአብሔር ይረዳናል፡፡ ፈረንጅ ይረዳናል ብለን መጠበቁ አያዋጣም፡፡ የቤት ስራዎቻችንን ለመስራት እንሞክራለን፤ እናንተም የቤት ስራዎቻችሁን ስሩ ነው ያልኩት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተገቢ ዲፕሎማሲያዊ ጫና አድርጉ፡፡ ገንዘቡን (ቼኩን) ስትሰጡ ዝም ብላችሁ ሣይሆን ይሄ ገንዘብ የት እየደረሰ መጠየቅ አለባችሁ፡፡ ለሕዝቡስ እየደረሰ ነው ወይ ብቻም ሣይሆን ከዛም አልፋችሁ፣ ስለእስረኞች ጉዳይ፣ ስለሰብዓዊ መብት ረገጣ ጉዳይ፣ ስለፖለቲካ መድሎ ጉዳይ፣ ነፃ ፍትሐዊ ምርጫ፣ ስለሚዲያ ጉዳይ ጠይቁ የሚሉ ነገሮችን አንስቻለሁ፡፡ እኛም የራሣችንን የቤት ስራ መስራት አለብን፡፡ እናንተም ደግሞ የቤት ስራዎቻችሁን መስራት አለባችሁ፤ ዝም ብላችሁ ብቻ ቼክ መፃፍ አይደለም የሚለውን በአጭሩ ቅልብጭ ባለ ቋንቋ ለመናገር ሞክረናል፡፡ ሎሚ፡- ወ/ሮ አና ጐሜዝ ስለ ጠ/ሚ መለስ የነገሯችሁን ለኢህአዴግ ባለስልጣናት የገለፁላቸው ይመስልዎታል; ዶ/ር መረራ፡- እርግጠኛ አይደለንም፡፡ ከአፈ-ጉባኤ አባዱላ ጋር የተነሣችሁን ፎቶ ሪፖርተር የተባለ የኢህአዴግን ልብ እያየ የሚፅፍ ጋዜጣ ላይ አይቻለሁ፡፡ ምን እንደተባባሉ አላውቅም፡፡ ምን እንደተባባሉ እነሱ ነው የሚያውቁት፡፡ አልጠየቅንምም፡፡ እንደአስፈላጊ ነገርም አላየሁትም፡፡ ሎሚ፡- ከእናንተ ጋር ውይይት ያደረገው የአውሮፓ ፓርላማ ቡድን ለኢትዮጵያ መንግስት/ኢህአዴግ ያለው ዕይታ ምን ዓይነት ነው; ዶ/ር መረራ፡- አውሮፓ ህብረትም ሆነ አሜሪካኖች ተቃዋሚዎች የኢህአዴግን መንግስት ከስልጣን ሊያወርዱ ይችላል ብለው ማመን አለባቸው፡፡ በዚህ ላይ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከነሱም ሆነ ከእነሱ ምሁራን ጋር ስንወያይ የተቃዋሚውን መከፋፈል ደጋግመው ያነሱታል፡፡ ያ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ እናንተ ኢህአዴግን አንቃችሁ ከስልጣን ለማውረድ መዘጋጀት አለባችሁ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የእነሱን ወዳጅነትና ድጋፍ የምንሻውን ያክል የእሣራችን የቤት ስራዎች የመስራት ግዴታ አለብን፡፡ በእኔ በኩል በተገቢው መንገድና ደረጃ እየሰራን አይደለም የሚል አቋም አለኝ፡፡ ላለፉት 20 አመታት የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የቤት ስራዎችን መስራት አልቻሉም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካን ወደፊት የመሄድና ያለመሄድ የሚወሰነው እሱ ነው፡፡ የጋራ አጀንዳ ቀርፀን፣ ይህንን የጋራ አጀንዳ ገንብተን፣ አቅም በፈቀደ መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ይዘን ወደፊት መግፋት አለብን፡፡

No comments:

Post a Comment